መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – በ2013 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ 191.28 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 191.45 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ 100.09 በመቶ መመዝገቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የስምንት ወራት ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ24.63 ቢሊየን ብር ወይንም የ14.76% ዕድገት አሳይቷል ነው የተባለው፡፡
ይህም ከሀገር ውስጥ ታክስ 116.70 ቢሊየን ብር፣ ከውጭ ቀረጥና ታክስ 74.59 ቢሊየን ብር እና ከሎተሪ ሽያጭ የተጣራ ገቢ 154.46 ብር ሚሊየን የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የገቢ አሰባሰብ ከነበረውና ካለው ዓለም አቀፋዊና ሀገር አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ከፈጠረው ኢኮኖሚዊ ተግዳሮት አንጻር ሲታይ የተሻለ አፈጻፀም የተመዘገበበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡