በ9 ወራት ከዲያስፖራው ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አጀንሲ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 37 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ በገንዘብና በአይነት ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቋል።

የኤጀንሲው ማኔጅመንት ባደረገው ውይይት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዲያስፖራ ማኅበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን የገመገመ ሲሆን ቀጣይ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት የዲያስፖራውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ 876 የበይነ መረብና የገጽ ለገጽ ውይይቶች መካሄዳቸው፣ 97 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው 1 ሺሕ 489 ዳያስፖራ አባላት የተለያዩ ድጋፎች መሰጠታቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም 5 ሺሕ 965 የዲያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንቶችን በመክፈት 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ማድረጋቸው እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲጨምር በተደረገ ክትትልና ድጋፍ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ቤት መላኩ ታውቋል።

ለኅዳሴው ግድብ ግንባታ ዳያስፖራው ከ122 ሚሊዮን ብር በላይ በስጦታና በቦንድ ግዥ ማሰባሰቡ፣ ለኅልውና ዘመቻው 109 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር፣ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍና ለተጎዱ መሰረተ ልማቶች ግንባታ በጥሬ ገንዘብ 777 ነጥብ 35 ሚሊየን ብር፣ በአይነት 336 ነጥብ 26 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW