ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ 11 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ለማሰማራት መዘጋጀቱን አስታወቀ።
6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ከቅድመ ምርጫ አንስቶ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ተብሏል።
የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ በምርጫው ለመሳተፍ ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል የወጣቶች ማህበር አንዱ መሆኑን አስታውሶ፣ ማህበሩ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች የድርሻውን አስተዋፅኦ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሷል።
ዘንድሮም ምርጫው ሰላማዊና ስኬታማ እንዲሆን ለህብረተሰቡ በምርጫ ሂደት ላይ በየጊዜው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአማራ ወጣቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ሀገር የሱፍ በበኩሏ ከዚህ ቀደም በምርጫ ወቅት ሲከሰቱ ነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ለወጣቱ ግንዛቤ እንዲኖረው መደረጉን ተናግራለች።
ወጣቶቹ ለምርጫው ሰላማዊነት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውጭ ገለልተኛ ሆነው እንደሚንቀሳቀሱም ገልጻለች፡፡
ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ አገርን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቀጣል የበኩሉን እንዲወጣ የማስገንዘብ ሥራ መሰራቱን አመልክታለች።
“በቅድመ ምርጫ ወቅት ዜጎች ምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የተለያዩ ስራዎችን አከናውነናል” ያለው ወጣት ይሁነኝ፤ በምርጫው ዕለትም መራጮች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጿል።
ምርጫውን ሰላማዊና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ከቅድመ ምርጫ በፊት የሚሰሩ ሥራዎች ወሳኝነት እንዳላቸው ገልጾ፤ በማህበሩ ሥር የሚገኙ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በምርጫው እለት በታዛቢነት እንደሚሳተፉም ጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ የወጣቶች ግንዛቤ እና ተሳትፎ ማካተት ዳይሬክተር አቶ ጤናዬ ታምሩ በበኩላቸው፣ በምርጫ ህግ እና ስነ ምግባር አዋጅ ዙሪያ ለወጣቶች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዐቃቤ ህግ ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አገራዊ ምርጫው ሰላማዊና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ቢሮው ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ 11 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ለማሳተፍ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል፡፡
በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞችን የሚያስተባብሩ 220 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዳሉም ነው ያመለከቱት፡
ምርጫው በሰላምና በስኬት እንዳይጠናቀቅ የተለያዩ አካላት የሚያደርጉትን የጥፋት እንቅስቃሴ በመከላከል በኩል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡