ቢሮው በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች እውቅና ሰጠ

የካቲት 13/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች እውቅና ሰጠ።

ቢሮው ከተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ በመዲናዋ ለተለያዩ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶችም እውቅና በመስጠት ላይ ይገኛል።

በመዲናዋ 12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስክ 117 ተማሪዎች 600 እና ከዛ በላይ ከፍተኛ ውጤት ሲያመጡ በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ደግሞ ስምንት ተማሪዎች 500 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣታቸው በመድረኩ ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ 125 ተማሪዎች በተፈጥሮ እና ማህበራዊ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ማምጣት መቻላቸው ተገልጿል።

በእውቅና አሰጣጥ መርኃ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የትምህርት ዘርፍ አብይ ተልዕኮ ውጤት እንዲያመጡ እና እንዲያበረታቱ ማድረግ መሆኑን ገልጸው ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ መምህራን፣ የትምህርት ተቋማት እና ወላጆች ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ያሉት ኃላፊው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ እንደሆነ አመላክተዋል።

በመዲናዋ ከተፈተኑ 47 ሺሕ 970 ተማሪዎች መካከል ከ9 ሺሕ 900 በላይ ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ያመጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ 20 ትምህርት ቤቶች ውስጥም አስሩ በመዲናዋ የሚገኙ እንደሆነ ተናግረው ይህም ውጤት ለ2015 ትምህርት ዘመን በትጋት እንድንሰራ የሚያደርገን ምቹ መደላድል የፈጠረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ ለተማሪዎቹ የእውቅና ሽልማቱን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግራቸው ትምህርት የችግር መፍቻ ቁልፍ መሆኑን ገልጸው የእድገት መሰረት የሆነው ትምህርት በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ትልቅ የቤት ስራ ሰጥቶን ያለፈ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለሽልማት የበቃችሁ ተማሪዎች ለኛ እንቁዎቻችን ናችሁ ያሉት  ከንቲባዋ የግል ጥረታችሁ  ከፍተኛ ውጤት እንድታመጡ አድርጓቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በሱራፌል መንግሥቴ