ቢሮው የትንሳዔ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በመጠናቀቁ ለህብረተሰቡና ለባለድርሻ አካላት ምስጋና አቀረበ

 

ሚያዚያ 17/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የትንሳዔ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በመጠናቀቁ ለህብረተሰቡና ለባለድርሻ አካላት ምስጋና አቀረበ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) የትንሳዔ በዓል በሰላም እንዲከበር አስተዋፅዖ ላደረጉ አካላት፤ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት፤ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ለአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፤ ለአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሰራተኞችና አመራሮች፤ ለአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን፤ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች፤ ለህዝባዊ ሰራዊት አባላት፤ በአጠቃላይ ለሰላም ወዳዱ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኃላፊው ጨምረውም በቀጣይ ሳምንትም የኢድ አልፈጥር በዓል ስለሚከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የኢድ አልፈጥር በዓል ከወትሮ ለየት ባለ መልኩ የሚከበር ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት በሚል መሪ ቃል በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትየጵያዊያን በዓሉን ለማክበር ወደ አገር ቤት እንደሚመጡ አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ልዩ ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ለተለመደ ትብብራቸው እንዲዘጋጁ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላቷል፡፡