ቢቢሲ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚገባው በላይ እያራገበ ነው ሲል የዘ ኢኮኖሚስት አርታኢ ተቸ

ኅዳር 3/2014 (ዋልታ) ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ወግኖ አገር ለማፍረስ የሚታትረው የእንግሊዙ ቢቢሲ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚገባው በላይ እያራገበ ነው ሲል የዘ ኢኮኖሚስት ጋዜጣ የአፍሪካ አርታኢው ጆናታን ሮሲንታል ተቸ፡፡
ጋዜጠኛው ይህን ያለው ቢቢሲ በጂቡቲ ከሚገኘው የአሜሪካ ጦር መሪ ጋር ቃለ መጠይቅ አደርጎ ያቀረበውን ዘገባ ለአብነት በጠቀሰበት የቲውተር ጽሑፉ ነው፡፡
ካምፕ ሌሞኒየር የተሰኘው በጂቡቲ የሚገኘው ጦር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዊሊያም ዛና በቃለ መጠይቁ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የአሜሪካ ዲፕሎማትና ዜጎችን የማስወጣት ኃላፊነት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
ሜጀር ጄኔራሉ አክለውም ከኅዳሴ ግድብ እንዲሁም ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ያሉ አለመስማማቶችን አስታውሰው አንዳንድ አገራት የኢትዮጵያን አሁናዊ የውስጥ ጉዳይ እንደምቹ አጋጣሚ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉም አሳውቀዋል፡፡
ሆኖም ቢቢሲ የአሜሪካ ጦር በኢትዮጵያ ጣልቃ ገብቶ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ሆኗል ሲል ለፍላጎቱ የሚስማማውን ሀሰተኛ መረጃ ፈጥሮ አሰራጭቷል፡፡
የዘ ኢኮኖሚስቱ አርታኢ ስለቢቢሲ ያልተገባ የማራገብ አካሄድ ሲጽፍ ከተባለው አወድ ውጭ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ እየጠየቀ መሆኑን አሳብቆበታል ብሏል፡፡
የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያዊያን ከውስጥና ከውጭ የተሰበሰቡ ጠላቶች የከፈቱትን የተቀናጀ አገር የማፍረስ ዘመቻ እየቀለበሱት በየዕለቱም ድል እያስመዘገቡ ሲሆን፤ ለውጭ ጠላት ተላላኪ ሆኖ የግንባር ጦርነት የከፈተውንና አሁን ላይ ወደ ተመኘው ሲኦል ሊሸኝ ጫፍ የደረሰውን የሽብር ቡድን ግብኣተ መሬት ለማፋጠን ወደ ግንባር እየዘመቱ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ጣልቃ ገብተው የራስን ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚሹ አገራት ያሉትን ያክል የኢትዮጵያ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ጥበብና አቅምም ይፈቱታል የአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉኣላዊነት መጠበቅ የግድ ነው በሚል በፀጥታው ምክር ቤትም ጭምር ፅኑ አቋማቸውን እያሳወቁ ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ አገራት መኖራቸው አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአፍራሹ ሕወሓት ጎን የተሰለፉ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ጉዳይ በተጣመመ መንገድ እየዘገቡ መሆኑን ገልፆ እየተቃወመው ይገኛል፡