ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአካባቢው ወጣቶችና አርሶአደሮች ተጠቃሚነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

ጥቅምት 18/2016 (አዲስ ዋልታ) የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ከግምት ውስጥ በማስገባት በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ለአምራች አርሶ አደሮች እና ለስራ ፈላጊ ወጣቶች ተጠቃሚት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲን ፓርኩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በፓርኩ ውስጥ ከተጀመሩ ኢንቨስትመንቶች መካከል አንዱ የሆነው ኒርቫና አኩሪ አተር ለሚያመርቱ 10 ሺሕ አርሶአደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው በፓርኩ ውስጥ ስራ የጀመረው አፉላንስ ማኑፋክቸሪንግ ካምፓኒ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን በማምረት ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተጨማሪ ለተለያዩ የሀገሪቱ ከፍሎች ምርቶቹን በማቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኩባንያው ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የአካባቢው ወጣቶች ካላቸው ክህሎት ጋር ቴክኖሎጂን በፍጥነት በማዋሀድ ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም መግለፃቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ ጥሩዬ ቁሜ በበኩላቸው በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት አቅምና ፍላጎቱ ላላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሀብቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የማምረቻ ሼዶችና የለማ መሬት ዝግጁ ሆነው ባለሀብቶችን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡