ባለሀብቱ አይሸሽም ተካ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላስመዘገቡት ውጤት እውቅና እና ሽልማት ተበረከተላቸው

ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላስመዘገቡት የላቀ ውጤት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢውለደር የተሰኘ የሽልማት ድርጅት እውቅና እና ሽልማት አበረከተላቸው።

ባለሀብቱ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላስመዘገቡት የላቀ ውጤት በምዕራባዊት አፍሪካ ኮትዲቯር አቢጃን ከተማ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በክብር እንግድነት የተጋበዙት ባለሀብቱ ሽልማቱን ከቀድሞ የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር ፓስካል አፊኒጊሳን እጅ መቀበላቸውን ባለሀብቱ አይሸሹም ከዋልታ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳን ቆይታቸው በሰላም፣ ልማት እና ሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እ.ኤ.አ በ2019 ከደቡብ ሱዳን መንግስት የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸውም እንደነበር ይታወሳል።

የአፍሪካን ኢኮኖሚ በመገንባት ትልቅ ድርሻ ላበረከቱ ታዋቂ አልሚዎች እውቅና የሚሰጠው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢውለደር ሽልማት በዘንድሮ ለኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካን ጨምሮ ለ30 ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለተወጣጡ አልሚዎች እውቅና ሰጥቷል።

ላለፉት 15 ዓመታት ኑሯቸውን በደቡብ ሱዳን ጁባ አድርገው የተለያዩ የንግድ ስራዎችን በማከናወን የሚታወቁት ባለሀብቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በደቡብ ሱዳን እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ እያበረክቱ በሚገኘው ተሳትፎ ነው እውቅና እና የክብር ሽልማት የተደረገላቸው።

የተበረከተው እውቅና እና ሽልማት በቀጣይ ጠንክረው እንዲሰሩ ተጨማሪ ኃላፊነት የተጣለባቸው ያህል እንደተሰማቸው የገለፁት ባለሀብቱ ለዚህ እንዲበቁ ላደረጉ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ምስጋና ችረዋል።

ይህ ሽልማት አፍሪካዊያን ባለሀብቶች በቀጣናው ተንቀሳቅሰው እንዲያለሙ ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል።

እውቅናው የአፍሪካን ኢኮኖሚ በመገንባት ትልቅ ድርሻ ላበረከቱ ታዋቂ አልሚዎች እውቅና ሲሰጥ ይህ ለ12ኛ ጊዜ ነውም ተብሏል።

በሱራፌል መንግሥቴ