የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ባለፉት 6 ወራት 622 ሚሊየን ብር ከውሃ የአገልግሎት ክፍያ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች መሰብሰቡን ገለጸ።
በባለሥልጣኑ የጥናት ዕቅድና በጀት ሃላፊ በዓለምላይ ባህሩ በ2013 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 798 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የእቅዱን 78 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንጻር ዝቅ ቢልም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ13 ሚሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በባለስልጣኑ በስድስት ወራት ከ96 ሚሊየን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሂሳብ እንዳለ የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህም ውስጥ ከ50 ሺህ ብር በላይ ውዝፍ ያለባቸው 212 ደንበኞች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ባለስልጣኑ የዕለት ተዕለት ስራውን ለማከናወን በውስጥ ገቢ የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ የአገልግሎት ክፍያ የማይፈጽሙ ደንበኞች በስራው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን በመረዳት በአፋጣኝ ክፍያ እንዲፈጽሙ ማሳሰቡን ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።