ባለፈው በጀት ዓመት ከወርቅ ምርት ከ560 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

ሚኒስትር ዴኤታ ቶማስ ቱት

ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) በ2014 በጀት ዓመት ከወርቅ ምርት ከ560 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች የማዕድን ዘርፉ ለሌሎች ዘርፎች በተሰጠው ልክ ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን በማዕድን ሚኒስቴር የጂኦ ሳይንስና ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ቶማስ ቱት ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ ግን መንግስት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው በተለይም በወርቅ ማዕድን የሚታወቀው የጋምቤላ ክልል በስፋት ወርቅ በሚመረትባቸው አኝዋክ እና ማጃንግ ዞኖች ውስጥ ባሉ አራት ወረዳዎች ሐብቱን በተገቢው ጥቅም ላይ ለማዋል በሰፊው እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ያነሱት ሚኒሰትር ዴኤታው በሥራ ሥምሪት በአራቱም ወረዳዎች በእኩል ደረጃ የመንቀሳቀስ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር በርካታ የወርቅ ማዕድን እንደሚገኝባቸው የሚታወቁት የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሆኑም ያነሱ ሲሆን ጥናት ቢደረግ በሌሎች ክልሎችም ማዕድናት ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በክልሎች ሐብቱን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር ውስንነቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው ወርቅ እየተመረተ ያለው አድካሚና አሰልቺ በሆነ ባሕላዊ መንገድ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በዘርፉ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት አነስተኛ ነውም ብለዋል፡፡

ወጣቶች ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ በአራቱም ክልሎች በሚኒስቴሩ ፕሮጀክት በመቀረፅ የአደረጃጀት እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ዘርፉን መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካላትም ሊደግፉት ይገባልም ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!