ባለፉት ሶስት ወራት የ4 ሺሕ 628 አቅመ ደካሞች ቤት መታደሱን ከንቲባ አዳነች ገለጹ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) ባለፉት ሶስት ወራት ከ1 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እና ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ የ4 ሺሕ 628 አቅመ ደካሞችን እና የሀገር ባለውለታዎችን የመኖሪያ ቤት ማደስ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2015 በጀት ዓመት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት ነጥቦችን አስመልክቶ በጉባኤው ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም፤ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እንዲያግዝም 1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 25 የዳቦ ፋብሪካዎችን እና 106 የዳቦ መሸጫ ሱቆች ግንባታ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በጋራ የመኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ጥንቃቄ የተሞላበት የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት በመከተል ለባለዕድለኞች ዕጣ የማውጣት ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከተማዋን ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 3 ሺህ 303 ሕገ-ወጦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።

ከሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ አዲስ የመታወቂያ አሰጣጥ እንዲቆም ቢደረግም 4 ሺሕ 649 በሕገ ወጥ መንገድ የተሰጡ መታወቂያዎች መያዛቸውን ያነሱት ከንቲባዋ፣ በዚህም በ90 አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ሌብነት እና ብልሹ አሠራር፣ የአቅም ውስንነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመሬት ወረራ እና ሕገ-ወጥነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በሩብ ዓመቱ ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ማለታቸውን የኢብኮ መረጃ አመላክቷል።

በሩብ ዓመቱ 60 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በ2015 በጀት ዓመት ከተማ አስተዳደሩ ለሕግ ማስከበር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ሪፎርም ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።