ባለፉት 10 ወራት ከ425 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ

ግንቦት 8/2016 (አዲስ ዋልታ) በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት 10 ወራት ከ425 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ በበጀት ዓመቱ 529 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው አፈጻጸሙ በታቀደው ልክ እየሄደ ነው ብለዋል።

ይህንን ለማሳካት ቀረጥና ታክስን በፈቃደኝነት የመክፈል ባህል ማሳደግ፣ የዲጅታል አገልግሎትን ማሳደግ፣ የታክስና የጉምሩክ አስተዳደር ፍትሐዊነትን ማረጋገጥና ሌሎች ስትራቴጂዎች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓመቱ የሚያዝያ ወር ከፍተኛ ገቢ የሚሰበሰብበት ሲሆን ከሀገር ውስጥ ታክስ፣ ከውጭ ቀረጥና ታክስ 51 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 51 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የ4 ነጥብ 91 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሯ በአጠቃላይ ባለፉት 10 ወራት 442 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 425 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስረድተዋል።

አፈጻጸሙም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ54 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር ወይም የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል።

ጠቅላላ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ የሀገር ውስጥ ታክስ ድርሻ 271 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ሲሆን 153 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር ደግሞ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ የተሰበሰበ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ በኩል ባለፉት 10 ወራት 49 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የተላለፈ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 ነጥብ 44 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።