የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀይማኖታዊ ክብረ በአላት በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ በድሬዳዋና አካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት የእውቅናና የምስጋና ሽልማት አበረከተች፡፡
ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች ኃይማኖታዊ ክብረ በአላት ያለ ፀጥታ ችግር እንዲከበር ላደረጉ የፀጥታ አካላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ፅህፈት ቤት የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።
በዚህም የምስራቅ እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የምስራቅ ኢትዮጵያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህና ፀጥታ ህግ ጉዳዮች ቢሮ በጋራ በመሆን ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ያደረጉት አስተዋጽኦ የላቀ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በተለይም ላለፉት ሶስት አመታት በነበረው የፀጥታ ችግር የፀጥታ አካላቱና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ በህዝበ ክርስቲያኑና በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም ሲሰሩ እንደነበር ተገልጿል።
በዚህም የፀጥታ አካላቱ ለፈፀሙት አኩሪ ተግባርና ለከፈሉት ዋጋ የምስጋናና እውቅና ሽልማት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተበርክቶላቸዋል፡፡
በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የፀጥታ ተቋማት ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን ደረጃ የሰሩትን ቅንጅታዊ ስራ አመስግነዋል።
በቀጣይም እንዲህ አይነት መልካም ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፀልያለን ብለዋል።
የእውቅናና የምስጋና ሽልማት የተበረከተላቸው የፀጥታ ተቋማት ሃላፊዎች በአላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የፀጥታ መዋቅሩ ከሀይማኖት ተቋማትና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በትብብርና በቅንጅት መስራታችን ነው ብለዋል።
ዕውቅናውም በቀጣይ ይበልጥ ህዝብንና ሀገርን በትጋትና በላቀ ጀግንነት ለማገልገል የሚያነሳሳና ሞራል የሚሰጥ ስለመሆኑ የፀጥታ ተቋማቱ ኃላፊዎች መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የፀጥታ አካላቱ ከእውቅና ሽልማት ስነ-ስርአቱ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እየሰራች ያለችውን የልማት እንቅስቃሴና የቤተክርስቲያኗን ሙዚየም ጎብኝተዋል፡፡