ቤቶች ኮርፖሬሽን የገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክትን እያስመረቀ ነው

ሰኔ 5/2014 (ዋልታ) የፌደራል ቤቶቸ ኮርፖሬሽን ያስገነባውን የገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት እያስመረቀ ነው፡፡

የገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር በግንባታ ኢንዱስትሪው ባልተለመደ መልኩ በ18 ወራት ውስጥ ግዙፍ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ገንብቶ ማጠናቀቅ የተቻለበት ነው ተብሏል፡፡

ይህ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር በሦስት ሄክታር ይዞታ ላይ የተገነባ ሲሆን 510 ቤቶችን የያዙ 16 ብሎክ ዘመናዊ አፓርትመንቶች ያሉት ነው፡፡

የቤቶቹ ዓይነት ደግሞ የስካይ ቪላ ዱፕሌክስ እና የአፓርትመንት ቤቶችን ያካተቱ ሲሆኑ ስፋታቸው ከ150 ካሬ ሜትር እስከ 500 ካሬ ሜትር የሚደርሱ ቤቶችን ያካተተ መንደር ነው፡፡

የመኖሪያ መንደሩ የደኅንነት ሥርዓት የተገጠመለት፣ ከ800 በላይ መኪና የመያዝ አቅም ያለው መኪና ማቆሚያ ስፍራ፣ የጋራ መጠቀሚያ አዳራሽ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ የአረንጓዴ ቦታና መናፈሻ፣ አምፊ ቴአትር፣ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ፣ የባስኬት እና ቮሊ ቦል ሜዳዎች፣ የልጆች መጫዎቻ ቦታና የመዋኛ ገንዳን ያካተተ ነው፡፡

ፕሮጀክቱን በብቃት የገነባው ሀገር በቀሉ ኦቪድ የኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን የአልሙኒየም ፎርወርክ ቴክኖሎጂ አቅራቢው ኩምካንግ ካይንድ ፣ የኮሪያው ዓለም ዐቀፍ ኩባንያ እና የዲዛይን አማካሪው የህንዱ ፓሪን ሳህ አርክቲክትስ በጥምረት የተሳተፉበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሰለሞን በየነ