ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ግንቦት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በምክክር በመፍታት ሰላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙኃን የላቀ ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ሚዲያ ለኢትዮጵያዊያን ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር ኢትዮጵያ ችግሮቿን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ አሁን ላይ በ10 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች 17 ሺሕ 210 ተወካዮች የተመረጡ ሲሆን የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በምክክር በመፍታት ሰላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙኃን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደት የመገናኛ ብዙኃን ለነበራቸው አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም የላቀ ሚናቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ለኮሚሽኑ ጥረት መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ሚናቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱንም በቅርቡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሄድ መሆኑ ታውቋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አስካሁን ከ6 ሺሕ 215 በላይ ተባባሪ አካላት ጋር መስራቱም ተገልጿል።