ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ይሰራል

ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ይሰራል
ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ይሰራል

የካቲት 22/2014 (ዋልታ) ፓርቲው በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባትና ዘላቂ ልማት እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ፡፡

የፓርቲው አንደኛ ጉባኤ “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ እና ማዕካለዊ ኮሚቴ አባላት ከሰሞኑ የተወያዩባቸውን ጉዳዮች በማስመልከት የኮሜቴው አባላት ብናልፍ አንዱዓለም እና ተስፋዬ ቤልጂጌ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ብናልፍ በመግለጫቸው በኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት የነበረው ትግል እና የለውጥ እንቅስቃሴ ብልጽግና ፓርቲ እንዲወለድ መሰረት ጥሏል ብለዋል፡፡

ለውጡን በየዘርፉ እየመራ እና ማሻሻያዎችን እያደረገ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የነበረው የኢህዴግ አደረጃጀት ወቅቱን ያልዋጀ መሆኑ በጥናት ተረጋግጦ አካታች ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ከመመስረት እስከ ሪዮተ ዓለም መሻሻያ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።

የለውጡን ሃሳብ ባለመቀበል እና በጥናቱ ውጤት ባለመስማማት ህወሓት በራሱ ፈቃድ ራሱን ማግለሉንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታትና የህዝቡን ጥቅም በማስቀድም በየዘርፉ ለውጥ በማድረግ የተሻለ ራዕይ ይዞ የተነሳው ብልጽግና ፓርቲ እውነተኛ የዴሞክራሲ እና የልማት አጀንዳዎችን ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

ከዴሞክራሲ አኳያም የመግባባት ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚል አቋም ላይ በመደረሱም ያንን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በቀጣይም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተስፋዬ ቤልጂጌ በበኩላቸው የፓርቲው ማዕከላዊና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን እያጋጠሟት ባሉ አገራዊ ተግዳሮቶች ዙሪያ በመወያየትም የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ በጉባኤውም ቀርበው ወይይት እንዲካሄድባቸው በመወሰን መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡

የጉባኤውም ዋነኛ ዓላማ ያለፉትን ዓመታት የለውጥ ጉዞ በጥልቀት በመገምገም የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ የሚካሄድ ጉባኤ መሆኑን ጠቅሰው ጉባኤው በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮች እልባት በሚያገኙባቸው የመፍትሄ አማራጮች ላይ ይመክራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧ፡፡

በጉባኤው ከ38 አገራት የተጋበዙ 41 የብልጽግና እህት ፓርቲዎች ልዑካን የሚታደሙ ሲሆን 1 ሺህ 600 የብልጽግና አባላት በድምጽ እንዲሁም 400 ተጋባዥ እንግዶች ያለ ድምጽ ይሳተፉበታል ተብሏል።