ብልጽግና ፓርቲ ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ልማት ማፋጠን የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ ነው

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የጋምቤላ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች “አዲስ ፓለቲካዊ እይታ፣ አዲስ ሀገራዊ እመርታ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በጋምቤላ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀመረ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል ኡሞድ ኡጁሉ ስልጠናው በክህሎትና በልምድ የዳበረና እንደ ሀገር የተጀመረውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችል አመራር ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተጀመረው የአቅም ግንባታ ስልጠና እስከ ወረዳ ለሚገኙ አመራር አካላት ድረስ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው በቀጣይ ለሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች አቅም የሚፈጥር ስለሆነ ሰልጣኞቹ ስልጠናውን በንቃት እንዲከታተሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ላድር ላክባብ በበኩላቸው ስልጠናው ብልሹ አሰራሮችን በመታገል የክልሉን ልማት ማፋጠን የሚያስችል አመራር ለመፍጠር ታሰቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከ200 መቶ በላይ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።