ብልጽግና ፓርቲ ከዓለም አቀፍ የምርጫ የታዛቢዎች ቡድን ጋር ተወያየ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – ብልጽግና ፓርቲ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሚካሄደውን ሃገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ከዓለም አቀፍ ሪፐብሊካን ተቋም እና ከብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋም የጋራ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ጋር ተወያየ፡፡
በውይይቱ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ብልጽግና ፓርቲ ወጥ ሃገራዊ ፓርቲ ሆኖ፥ አካታችና አቃፊ በሆነ መንገድ ራሱን በማደራጀት በአዲስ እሳቤ፣ መዋቅር፣ ፕሮግራምና አሰራር ወደ ስራ መግባቱን ለቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡
ፓርቲው ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ያካተት መሆኑን ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አስገንዝበዋል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎችን ለቡድኑ አባላት ያብራሩ ሲሆን በኢትዮጵያ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሳካና ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ እንዲረጋገጥ ፓርቲው አበክሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመልካም ትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ያወሱት ዶክተር ቢቂላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሚና በብቃት በመወጣት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ቡድን አባላትም በተሰጠው ማብራሪያ ቅድመ ምርጫውን አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና ይህም ቀጥሎ ለሚያደርጉት የምርጫ መታዘብ ተልዕኳቸው እንደሚያግዛቸው መግለፃቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላከታል፡፡