ሚያዝያ 23/2013 (ዋልታ) – በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የእጩዎች ትውውቅና የምርጫ ቅስቀሳ መርሐግብር ተካሄደ፡፡
“በወንድማማችነት እሴት ላይ የተመሠረተ ህብረብሄራዊ አንድነት በመገንባት ሀገራዊ ብልጽግናችንን እውን እናደርጋለን” በሚል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የእጩዎች ትውውቅና የምርጫ ቅስቀሳ መርሐግብር ተካሄደ፡፡
በመርሐግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ ለህዝብ ተወካዮችና ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ እጩዎች ተገኝተዋል።
ከተማዋን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በማሳደግ ለሁሉም ነዋሪዎች የተመቸች የብልጽግና ተምሳሌት የሆነችው ከተማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
በከተማዋ ከእንጦጦ ፓርክ ጀምሮ የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ እና ለቱሪስት መስህብ የሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል ፤በቀጣይ ቀናትም የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች አሉ ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡