ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተው የአገልግሎት መቋረጥ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

መጋቢት 8/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተው የአገልግሎት መቋረጥ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን እንዳረጋገጠ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ብሔራዊ ባንኩ በችግሩ ምክንያት የተከሰቱ የደንበኞች መጉላላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ወደፊት ለህብረተሰቡ የሚያሳውቅ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሟቸውን ሥርዓቶች ደህንነታቻው የተጠበቀ፣ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉ ስለመሆናቸው በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት በጊዜያዊነት መቋረጥን አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ሰዓታት መቋረጣቸው ይታወቃል፡፡

እንደሚታወቀው ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ባንኮች በሥርዓቶቻቸው ላይ በየጊዜው የደህንነት ፍተሻ እንዲሁም የማሻሻያ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ በሥርዓቶቹ ላይ በሚከናወን ለውጦችና ፍተሻዎችም የባንኮች አገልግሎት አልፎ አልፎ ሊቋረጥ ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትናንትና ዕለት የተከሰተው የአገልግሎት መቋረጥ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ችግሩ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የባንኩን እና የደንበኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በመሆኑም የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጀምሩና ባንኩ ወደተለመደው እንቅስቃሴው እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተው የአገልግሎት መቋረጥ ባንኩ በመደበኛነት በሥርዓቶቹ ላይ በሚያደርገው ማሻሻያና ፍተሻ ምክንያት የተከሰተ እንጂ የባንኩን፣ የደንበኞቹን እንዲሁም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በችግሩ ምክንያት የተከሰቱ የደንበኞች መጉላላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ወደፊት ለህብረተሰቡ የሚያሳውቅ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሟቸውን ሥርዓቶች ደህንነታቻው የተጠበቀ፣ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉ ስለመሆናቸው በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸው የተጠበቀ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም መቀጠል ይችላል፡፡

የፋይናንስ ተቋማትም የሥርዓቶቻቸውን ደህንነትና ቀልጣፋነት ይበልጥ ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭ ባህርይ በማየት በቀጣይነት መሥራት እንደሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደህንነት የበለጠ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጠል አስፈላጊ እርምጃዎችንና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን መውሰዱን ይቀጥላል።