ብሔራዊ የተሐድሶ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በመቀሌ መካሄድ ጀመረ

መጋቢት 1/2015 (ዋልታ) መንግሥትና ህወሓት የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ትግበራ አካል የሆነው ብሔራዊ የተሐድሶ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ዛሬ በመቀሌ መካሄድ ጀምሯል።

መድረኩን ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱም ነው የተገለጸው።

በመድረኩ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አመባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ምክትል ኮሚሽነር አትንኩት መዝገቡ (ዶ/ር)፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴራል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የሕወሓት አመራሮች፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ ቱርሃን ሳለህ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና የልማት አጋሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የውይይት መድረኩ ዋነኛ ትኩረትም በኮሚሽኑ ተልዕኮዎች አደረጃጀትና የቀጣይ ሁለት ዓመታት የፕሮግራም ዋና ዋና ተግባራት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከርና መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የሰላም ስምምነቱ አካል የሆነውን የቀድሞ ተዋጊዎች ዘላቂና ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ ለማድረግ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ለማሳየት ነው ተብሏል።

በዚህም የኮሚሽኑ ዓላማዎች፣ ዋና ዋና ግቦችና የቀጣይ ሥራዎች ላይ በመወያየት የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና በመስኩ የአገር ውስጥና የውጪ ልምዶችን ለመጋራት ነው የተባለው።

የተሐድሶ ኮሚሽኑ የመጀመሪያ ምክክሩን በመቀሌ እንዲካሄድ ያደረገው የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩንና በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን መጎልበቱን ለማረጋገጥ መሆኑም ተነስቷል።

መንግሥት አገራዊ የትግበራ አድማስ ያለውን “ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2015” አቋቁሟል።

ኮሚሽኑ በዋናነት መንግስት ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል  ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ይሰራል።

የኮሚሽኑ ተልዕኮ በአንድ ተቋም ተጀምሮ የሚያልቅ ሳይሆን የብዙ አካላትን ቅንጅት፣ ትብብርና አጋርነት የሚጠይቅ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግሥትና ህወሓት በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ውስጥ አንዱ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል መልሶ የማቋቋም ሂደትን የሚመለከት መሆኑ ይታወቃል።