ብሔራዊ ጥቅም የሚነኩ ዘገባዎችን የማጋለጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ዓለም አቀፍም ሆኑ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የሚያወጧቸው ሉዓላዊነትን የሚዳፈርና የአገርን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዱ መረጃዎችን የማጋለጥ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የማህበሩ የሥልጠና ክፍል ኃላፊ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሙጬ አንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ አገራትና ተቋማት ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገዋል።

በተለይ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሚታይባቸው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን እንዲሁም ወደ ሽብር ተግባር ሊከቱ የሚችሉ መረጃዎችን እያወጡ ይገኛሉ ብለዋል።

ይህ ትክክል እንዳልሆነ ማህበሩ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ወደፊትም የአገርን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዱ ሆነው የሚገኙ መረጃዎችን የማጋለጥ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢፕድ ዘግቧል፡፡