ብሪታኒያ ከደቡብ አፍሪካ የገባ አዲስ የኮሮና ዝርያ ስጋት ውስጥ ጥሎኛል አለች

ታላቋ ብሪታኒያ አዲስ የኮሮና ዝርያ ያለባቸው 2 ሰዎችን ማግኘቷን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ማት ሐንኩክ አስታወቁ።

በሎንዶንና በሰሜን ምዕራብ ኢንግላንድ የተገኙት ሁለቱ ሰዎች ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው ከነበሩ ሰዎች ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተረጋግጧል።

ባለፉት 15 ቀናት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው የነበሩ ዜጎች ወይም ከደቡብ አፍሪካ ከመጣ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው በሙሉ በአስቸኳይ ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ አደራ ተብለዋል።

ይህ አዲስ ዝርያ ሰሞኑን በ70 ከመቶ ፍጥነት የመዛመት ጉልበት አለው ከተባለ ሌላ ዝርያ ጋር የሚያያዝ አይደለም።

የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር ዝዌሊ ምሂዜ ይህ አዲስ ዝርያ አዲስ ጭንቀት ወልዷል ብለዋል። ወጣትና በጣም ጤነኛ የሆኑ ሰዎችን ጭምር የሚያንበረክክ ዝርያ እንደሆነም አብራርተዋል።

ጤና ሚኒስትሩ ሲናገሩ “ደቡብ አፍሪካ ኤችአይቪ የመጣ ሰሞን የሆነችውን ዓይነት ምስቅልቅል ውስጥ አሁን ልትገባ አይገባትም’ ሲሉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያድርጉ ብለዋል።

ይህ ዝርያ ከተገኘ ወዲህ ሆስፒታሎች አካባቢ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ በሆነ አደገኛ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ጤነኛና ወጣት የሆኑ ሰዎች ጭምር መሆኑ ነገሩን አሳሳቢ አድርጎታል።