“ብራይት ፊውቸር ኢን አግሪካልቸር” በተሰኘ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በብዙ ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሆነች ተገለጸ

የካቲት 28/2015 (ዋልታ) ላለፉት አራት ዓመታት በተተገበረ “ብራይት ፊውቸር ኢን አግሪካልቸር” በተሰኘ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በብዙ ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሆነች ተገለጸ፡፡

ፕሮጀክቱ በተለይ የኢትዮጵያን የግብርና ሙያ ትምህርት ዘርፍን ለመደገፍ ያለመ በኔዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚደገፍ ነው፡፡

የብራይት ፊውቸር ኢን አግሪካልቸር ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሁብ ሙድሌ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ እና የወተት ተዋጽኦ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የአመራር እና አስተዳደር፣ ሥራ ፈጣሪነት እና የቢዝነስ ፕላን አነዳደፍን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ለ808 ኢትዮጵያዊያን ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው ስራ ፈጣሪዎችን፣ አስተማሪዎችን፣ ተማሪዎችን፣ አርሶ አደሮችን እንዲሁም በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ ሰልጣኞችን ያካተተ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የግብርና ልማትን በማነቃቃት ቀጣይነት ያለው የምግብ ስርዓት ለመፍጠር በስኬት የተተገበረ መሆኑን በመግለጽም ሀገራቸው ኔዘርላንድ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር መሰል የትብብር ፕሮጀክቶችን አጠናክራ እንደምትቀጥል ዳይሬክተሩ አክለውም ገልጸዋል፡፡

በብርሃኑ አበራ