ብቁ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) በ2014 በጀት ዓመት ብቁና ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር በተሰሩ ስራዎች አበረታች አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን በአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ባለስልጣኑ በ2014 በጀት ዓመት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በመጠቀሚያ ፈቃድ፣ በመሰረተ ልማት ቅንጅት እና ሌሎች ዘርፎች የተቋሙን መሪ ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ ብቁና ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር በተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ አፈጻጸሞች ተመዝግበዋል ብሏል፡፡

በመዲናዋ ብቁና ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ለ4 ሺሕ 639 የስራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች እና ባለሙያዎች የምዝገባና ፈቃድ እንዲሁም ለ44 የኮንስትራክሽን መሳሪያ አከራዮች የምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች በተሰጣቸው የብቃት ማረጋገጫ መሰረት መስራታቸውን ክትትል ከማድረግ ጋር ተያይዞ በ375 የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ላይ ክትትል ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ከዕቅድ በላይ በማሳካት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ከተማው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን መረጃ አመላክቷል፡፡

በ2015 በጀት ዓመትም ከዚህ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ቅንጅታዊ አሰራር መዳበር እንዳለበት ባለስልጣኑ አሳስቧል፡፡