ቦርዱ በሶማሌ ክልል የተካሄደውን የመራጮች ምዝገባ አስመልክቶ ያካሄደውን ምርመራ ሪፓርት አቀረበ

ነሀሴ 12/2013 (ዋልታ) – ምርጫ ቦርድ በሶማሌ ክልል የተካሄደውን የመራጮች ምዝገባ አስመልክቶ በአጣሪ ባለሞያዎች ያካሄደውን ምርመራ ሪፓርት ለፓርቲዎች አቀረበ፡፡

ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተካሄደውን የመራጮች ምዝግባ አስመልክቶ በባለሞያዎች አጣሪ ቡድን አጣርቷል፡፡

የቦርዱ ሁሉም አመራሮች የተገኙበት የምክክር መድረክ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎም በምክትል ሰብሳቢው ውብሸት አየለ አወያይነት በምርምራ ላይ ከተሠማሩት ዘጠኝ ቡድኖች ተወካዮች ቀርበው በየምርጫ ክልሎቹ ያደረጉትን ምርመራ ሂደት፣ ውጤት እና ለቦርዱ የሚያቀርቡትን የውሳኔ ሃሳብ አስረድተዋል።

በምርመራ ሂደቱም በቀረቡት ቅሬታዎች ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ግለሰቦች ጋር ባደረጓቸው ቃለመጠይቆች፣ በመሥክ ጉብኝት፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ በሰበሰቧቸው መረጃዎች፣ ከፎቶና ከተንቀሳቃሽ ምስል እንዲሁም የቀረቡ የተለያዩ የሠነድ ማስረጃዎችን በመጠቀም ያጠናቀሩትን ሪፖርት አቅርበዋል።

የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ከተሰማ በኋላ ቅሬታ ያቀረቡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሃሳብ እንዲሰጡ የተደረጉ ሲሆን፤ ፓርቲዎቹም ቅሬታዎቻቸውን እና ከቦርዱ የሚጠብቁትን የውሳኔ ዓይነት በተመለከተ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ቦርዱ በበኩሉ ውሳኔዎቹን ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች በቅርቡ እንደሚያሳውቅ በምክትል ሰብሳቢው አማካኝነት መግለፁን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።