ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በቡና ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቀቀ


ታኅሣሥ 16/2014 (ዋልታ)
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በቡና ሳይንስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
በቡና ምርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመመርመር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ባለመው የቡና ሳይንስ ትምህርት አጀማመር ላይ የመጨረሻው ውይይት በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የቡና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አለመሰጠቱን ጠቁመው በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመር መወሰኑ የቡና ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ታሪክ ሆኖ የሚነገር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ83 በመቶ በላይ ህይወታቸውን በግብርና የሚመሩ ዜጎች አገር በመሆኗ ከእርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ እንደ ቡናና እንሰት ባሉ ምርቶች ላይ መስራት አለብን ማለታቸውን የዩኒቨርሲቲው መረጃ አመላክቷል።
በዓለማችን በቀን አንድ ቢሊዮን ሰዎች ቡናን የሚጠቀሙ ስለመሆኑ በውይይት መድረኩ የተጠቀሰ ሲሆን ይህን ትልቅ ሃብት በትምህርትና ምርምር አስደግፎ መምራት ያስፈልጋል ተብሏል።