ተመራቂዎች አገራቸው ከገባችበት ወቅታዊ ችግር እንድትወጣ የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው ተባለ

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በጤናው ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 229 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡
የምርቃቱ የክብር እንግዳና የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ተመራቂዎች አገራቸው ከገባችበት ወቅታዊ ችግር እንድትወጣ የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለባትን የማኅበረሰብ ጤና ችግር ለመፍታት በሙያቸው እንዲያገለግሉ አደራ ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከገጠማት የጸጥታ ችግር እንድትወጣም የበኩላችሁን ድርሻ ማበርከት ይገባችኋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት 24 ሺሕ 500 ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብር እያስተማረ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በሌላ ዜና የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም ዩኒቨርሲቲው አገልግሎቱን ለማሻሻል ባለ 8 ወለል ህንጻ እየገነባ መሆኑን ገልጸው ከ5 ሺሕ በላይ አልጋዎች እንደሚኖሩት ጠቁመዋል፡፡
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በነገው ዕለትም በሻሸመኔ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ያስመርቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በፍሰሃ ጌትነት (ከመደ ወላቡ)