ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት ሥራ ላይ በማዋል ለማኅበረሰብ ለውጥ መሥራት አለባቸው -ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

ሰኔ 29/2016 (አዲስ ዋልታ) ተመራቂዎች በዩኒቨርዘሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ሥራ ላይ በማዋል ለማኅበረሰብ ለውጥ መሥራት እንደሚገባቸው የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገነዘቡ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 74ኛው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የለውጥ ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው በአንድ ዓመት እንዲጨምር መደረጉን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና አሠራር መጀመሩ ከለውጥ ሥራዎች መካከል መሆኑን አንስተዋል።

ተመራቂዎች ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ከግብ እንዲደርስ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነጎ (ዶ/ር) ናቸው።

መቱ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መርሃ ግብር ያሳለጠናቸውን 1 ሺህ 44 ተማሪዎች አስመርቋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል ዲማ ነጎ (ዶ/ር) ተመራቂዎች አገር የያዘችው የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

አገር የሚገነባው በተማረና በዕውቀት በዳበረ እንዲሁም በመልካም ስነ-ምግባር በጎለበተ ዜጋ መሆኑንም አንስተዋል።

በተመሳሳይ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺሕ 102 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመራቸው የምርምር ስራዎች አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ መሆናቸውን በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የሰው ሃይል ማፍራት የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።