ተቋሙ የቡና ጥራት ደረጃን በማሻሻል የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

መስከረም 28/2017 (አዲስ ዋልታ) የቡና ጥራት ደረጃን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ባለፉት ሦስት ዓመታት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ቡናን በክላስተር ማምረት እና ያረጁ የቡና ተክሎችን የመጎንደል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ባለፉት ሦስት ዓመታት 400 ሺህ ሄክታር የቡና ማሳ የተጎነደለ መሆኑን እና በአሁኑ ወቅትም ምርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 326 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ አመርቂ ቢሆንም ከጥራት አንጻር ግን መሻሻል የሚገባው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ቡና ጥራት 1ኛ ደረጃ 13 በመቶ ብቻ ሲሆን ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የጥራት ደረጃ አራተኛ እና አምስተኛ መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡

ይህም በዋጋ ደረጃ ሲታይ 50 በመቶ ቅናሽ ስላለው ሀገር ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ቡና የጥራት ደረጃ ወደ አንደኛ እና ሁለተኛ ከፍ በማድረግ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት እየተሰራ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።