ተቋርጦ የነበረውን ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ የማስመለስ ስራ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) ለጊዜው ተቋርጦ የነበረውን ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ የማስመለስ ስራ ለማስቀጠል ብሔራዊ ኮሚቴው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አስታውቀዋል።

ከሳዑዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የማስመለሱን ስራ እንደገና ለማስጀመር፣ በሚኒስትር ዴኤታዎ እና በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም በጋራ የተመራና ከተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ የብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባላትን የያዘ ቡድን በተመላሾች ጊዜያዊ መጠለያዎች ጉብኝት አድርጓል፡፡

አምባሳደር ብርቱካን መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማስመለስ ተግባራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።

ጉብኝቱ፤ ዜጎችን የማስመለሱን ሥራ ለማስቀጠል፣ በየመጠለያዎቹ ለተመላሾች መሠረታዊ አገልግሎት የሚሆኑ የግብዓት አቅርቦት ስለመሟላቱ፣ ለተመላሾቹ ሥልጠና ለመሥጠትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ስለሚቻልበት ሁኔታ እና መጠለያዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከ16 ባለድርሻ ተቋማት የተመሰረተው ብሔራዊ ኮሚቴ በማስተባበር በቅንጅት በተሰራው ሥራ በሳዑዲ አረቢያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከ71 ሺሕ በላይ ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለስ መቻሉን አስታውሰዋል።

በጉብኝቱ ላይ ሥራው የሚመለከታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሥራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን ዜጎችን በማስመለስ ስራው የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዜጎችን የማስመለሱ ስራ በሁለት ሳምንት ጊዜ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።