መጋቢት 10/2013 (ዋልታ) – ዘንድሮ በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ከጥላቻ ንግግር በመቆጠብ በሥነ ምግባር፣ ጨዋነትን በተላበሰ፣ አገርን ባስቀደመና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ሊተገብሩ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመለከቱ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የምርጫ እስትራቴጂና ማኔጅመንት ኮሚቴ አባል አቶ እዮብ መሳፍንት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚገነባ ምርጫ እንዲሆን ሁሉም ኃላፊነት አለበት።
“ምርጫው ከኢዜማ በላይ ነው፣ ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ አገራዊ ጉዳይ ነው ብለን እናምናለን፣ በመሆኑም አገርን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመራ አካሄድ እንከተላለን፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን በሚያሳካና በሚተገብር መንገድ እንቀሳቀሳለን” ብለዋል።
ሌሎች ፓርቲዎችም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በተላበሰ፣ ለአገር ቅድሚያ በሰጠ መንገድ መንቀሳቀስ አለባቸው ብለን እናምናለን ያሉት አቶ እዮብ፣ ኢዜማ አሸንፎ አገር የምትወድቅ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤ አገር ካሸነፈች ግን እንደፓርቲ የመቀጠል ዕድል እንደሚኖረው አመልክተዋል።
የመንግስት ሥልጣን የያዘውና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በጨዋነትና ሥነ ምግባርን በተላበሰ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፤ ይህንን ማድረግ ከተቻለ በኢትዮጵያ የተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ከፍ ያለ ዕድል እንደሚኖር ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ተስፋ ያለበት፤ በአንጻሩ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የጸጥታ ስጋቶች የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተው፤ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ማምጣትና አገርን ወደተረጋጋ ሁኔታ ማስገባት የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ኢዜማ የተረጋጋ ምርጫ እንዲሆን ተስፋ በማድረግ ለፓርቲው እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም አመራሩ ሊከተላቸው የሚገቡ የሥነ ምግባር መመሪያ አዘጋጅቶ ማሰልጠኑን ጠቁመው፣ ‹‹የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች በምንም አይነት መልኩ አገርን ወደ ችግር በሚከት ሁኔታ ውስጥ አይገኙም፤ ይሄንን አረጋግጠን ነው የምንጀምረው›› ብለዋል።
የእናት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያየህ አስማረ በበኩላቸው፣ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት አለን፣ በዚህም ሁላችንም አትራፊ እንሆናለን ብለዋል። ለትግበራው መንግሥት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃን ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ከግምት በጸዳ መልኩ የቀረበውን ሃሳብ ብቻ በመመዘን መምረጥ እንዲችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው፣ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል። በውጭና በአገር ውስጥ ተግዳሮቶች ባሉበት በዚህ ወቅት የምርጫ ቅስቀሳ ሲደረግ የጥላቻ ንግግር ማድረግ አገርን ወደ ከፋ ቀውስ ሊከት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የጥላቻ ንግግር ማድረግ ሕዝብን አለማክበር ነው፣ ለግጭት የሚዳርጉ ቃላቶችን መናገር አገሪቱንም ይጎዳታል ያሉት አቶ ያየህ፣ ያለውን ችግር በማቅረብ ውሳኔውን ለሕዝብ መተው ያስፈልጋል። ለሕዝብ ክብር ካለን፣ ለአገርም የምንቆረቆር ከሆነ ፖሊሲዎቻችንን አቅርበን ለመምረጥ ለሕዝብ ዕድል መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።
የሁሉም ፓርቲዎች ዋና ፍላጎት የተሻለ ሃሳብ ተመራጭ ሆኖ አገርን ቢያስተዳድር እጠቀማለሁ የሚል ሲሆን፣ በዚህ እሳቤ ከሰራን የመጨረሻው ግባችን አገር ማገልገል ይሆናል ብለዋል። ምርጫው በሰላማዊ መልኩ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ሕዝቡ የተሻለ አማራጭ መመልከት እንዲችል ሚዲያው ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለአድልዎ ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትና ህብረተሰቡ አማራጭ እንዲያገኝ ፓርቲዎች ለህብረተሰቡ የተሻለ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን የማቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክዋል።