ጥቅምት 11/2017 (አዲስ ዋልታ) ቲክቶክ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በሆነው ጊዜያዊ ሰራተኛ ምክንያት 10 ሚሊየን ዶላር አጥቷል መባሉን አስተባብሏል።
የቲክቶክ አስተዳዳሪ ድርጅት የሆነው ባይት ዳንስ አንድ የቲክቶክ ሰራተኛ በድርጅቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Generative AI) ላይ ያልተገባ አሰራር በመጠቀሙ ከድርጅቱ ማባረሩን ገልጿል።
ይሁን እንጂ በዚህ ምክንያት ድርጅቱ ከአስር ሚሊየን ዶላር በላይ አጥቷል ተብሎ በማህበራዊ ድረ ገጾች የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ባይት ዳንስ ይህን ድርጊት የፈጸመው ጊዜያዊ ሰራተኛ ድርጊቱን ሆን ብሎ እንዳደረገውና ከስራው ጋር የተያያዘ ምንም ልምድ እንዳልነበረው አመልክቷል።
ድርጅቱ ሰራተኛውን ከማባረር ባሻገር ለሚማርበት ዩኒቨርሲቲ ማሳወቁንም ገልጿል።
ነገር ግን ክስተቱ የድርጅቱ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ምንም ዓይነት ተጽእኖ አለማሳደሩን ባይት ዳንስ አስታውቋል። ጉዳዩም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አላግባብ ተጋኗል ነው ያለው።