ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ

ጳጉሜ 3/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ ገለጹ።

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን በጉባኤው ላይ ተገኝተው የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ያቀረቡት የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 88 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የኅዳሴ ግድብ በሁለት ዩኒት ኃይል ማመንጨት መቻሉ እና የግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የ2014 ወሳኝ ክንውኖች መሆናቸውን አስታውሰዋል።

እየታየ ላለው ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤቱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልፀው ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በ70 ቢሊዮን ብር ለማጠናቀቅ ታቅዶ የተጀመረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እስከ ሐምሌ 2014 ብቻ የወጣው ገንዘብ 172 ቢሊዮን ብር መድረሱን ማሳወቃቸውን ኢቲቪ ዘግቧል።

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በ2014 ብቻ በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያዎች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከኅብረተሰቡ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW