ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን የኤሌትሪክ ኃይል በዛሬው እለት ያመነጫል

የካቲት 13/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ 375 ሜጋ ዋት በሚያመነጨው ተርባይን የመጀመሪያውን የኤሌትሪክ ኃይል በዛሬው እለት ያመነጫል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በይፋ የግድቡን አንድ ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሥራ በይፋ እንደሚያስጀምሩ ይጠበቃል።

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ በግድቡ የግንባታ ሥራ ተሳትፎ የነበራቸውና አገራዊ አሻራን ያሳረፉ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች መርሃ ግብሩን ለመከታተል ከትናንት ጀምሮ ጉባ ገብተዋል።

የግድቡ 10ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት ሁለቱ ተርባይኖች ግንባታቸው ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር መንግሥት አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት የመረሰት ድንጋይ ካስቀመጠች አንድ ዓመት በኋላ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን በግድቡ ላይ ስጋት እንዳላቸው ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በግድቡ አስተዳደር ጉዳይ የሶስትዮሽ ንግግር እና ድርድር ከጀመሩ ቆይተዋል፤ ነገር ግን እስካሁን ከስምምነት አልደረሱም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡን እየገነባ ያለው ለልማት ዓላማ ብቻ መሆኑን እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የጎላ ተጽእኖ እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ግብጽና ሱዳን ግን በግድቡ ዙሪያ የየራሳቸው አቋም አላቸው፡፡

በተለይም ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመ ስምምነትን ጭምር በመጥቀስ፤ ታሪካዊ የሆነ የውሃ ድርሻዋ ላይ ተጽእኖ እንሚያሳድር እና ግድቡ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድርባት ትገልጻለች፡፡

በ2013 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሽንግተን ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ከፈረስ በኋላ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት እንዲካሄድ ተስማምተዋል፡፡

ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት የመጣው ኢትዮጵያ ድርድሩ ሳይጀመር የታዛቢነት ሚና የነበራቸው አሜሪካና የዓለም ባንክ ሚናቸውን ወደ አደራዳሪነትና የስምምነት ሰነድ አርቃቂነት ከፍ በማድረጋቸው እና ኢትዮጵያም ይህን አልቀበልም በማለቷ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የግድቡ ጉዳይ የልማት ጉዳይ ነው ብትልም ግብጽና ሱዳን የግድቡን ጉዳይ የጸጥታ ጉዳይ ነው በማለት ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በማቅረብ ምክር ቤቱ ወይይት አድርጎበት ያውቃል፡፡

(በአስታርቃቸው ወልዴ)