ታላቅ የኢትዮጵያዊነት ትዕይንት በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄደ

ሐምሌ 19/2013 (ዋልታ) – በአሜሪካን በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተቋቋመው ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር አስተባባሪነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሃብት ለማሰባሰብና ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማሳየት ታላቅ የኢትዮጵያዊነት ትዕይንት በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄደ።
አምባሳደር ፍጹም አረጋና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
አምባሳደር ፍጹም አረጋ ባስተላለፉት መልዕክት መድረኩን ላመቻቹት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ዳያስፖራው የጀመረውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራና ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
አክለውም ባለፉት አስር ወራት ብቻ በድር ኢትዮጵያ እያከናወነ ያለውን ሃብት የማሰባሰብ ሂደት ሳይጨምር በአሜሪካን ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በላይ መሰብሰቡን ገልጸው፣ በድር ኢትዮጵያም እስካሁን ያሰባሰበው ሃብት ከ785ሺህ ዶላር በላይ መድረሱን አስገንዝበዋል።
አምባሳደሩ እየተደረገ ስላለው ድጋፍ አመስግነው፣ ዳያስፖራው ከድጋፍ ባሻገር በራሱም ሆነ የሌሎችን አቅም በማስተባበር በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።
አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴም በበኩላቸው በመድረኩ ላይ እንዲሳተፉ በመጋበዛቸው አመስግነው፣ ዳያስፖራው ከሃገር ፍቅር በመነሳት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የተጀመረው ትግል አለመጠናቁቅን አንስተው፣ ዳያስፖራው ከድግቡም ሆነ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጥቅሞች አንጻር የሚያከናውናቸው ተግባራት ፍሬያማ እንዲሆኑ አንድነቱን በማጠናከርና ወዳጆችን በማብዛት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የሃይማኖት አባቶች ፣ ታዋቂ አርቲስቶችም ህዝቡን መገገኘታቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡