ታዳጊ ወጣቶችን በመጠቀም ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) ታዳጊ ወጣቶችን በመጠቀም የሽብር ተግባር ለመፈጸም በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ሁለት የሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጭሮ ከተማ ፀጥታ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጭሮ ከተማ ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሾይኢቢ ሀምዛ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የካቲት 27 ቀን 2014 ዓም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ነው።
ግለሰቦቹ ሰባት ታዳጊ ወጣቶችን “በጥሩ ክፍያ ስራ እናስቀጥራችኋለን” በሚል ከምዕራብ አርሲ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ጃራ ከተማ ሰባት ታዳጊ ወጣቶችን በማታ ወደ ጭሮ ከተማ ያመጧቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ታዳጊ ወጣቶቹን ወደ ከተማው ካመጧቸው በኋላ ወደ ጭሮ ወንዝ አካባቢ በመውሰድ ተልእኮ እየሰጧቸው ባሉበት ወቅት ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በጸጥታ አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ ከእይታ ለመሰወር ሲሉ ወደ ወንዝ አካባቢ ይዘዋቸው በመግባት በኅብረተሰቡ ውሰጥ ስለሚፈጽሟቸው ተግባራት ያስረዷቸው እንደነበር ወጣቶቹ መናገራቸውን ኃላፊው አመልክተዋል።
የታዳጊ ወጣቶቹ ቤተሰቦችም ከጃራ ከተማ ልጆቻችን በአንድ ቀን ጠፍተውብናል ሲሉ ማመልታቸውን ከከተማው ፖሊስ ማስረጋጃ መቅረቡንም ጠቁመዋል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው በጭሮ ከተማ ፖሊስ ምርመራ እየተደረባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአምስት ቀን በፊት ከሚኤሶ ከተማ ወደ ኦዳ ቡልቱም ወረዳ በለሊት ሰርገው ለመግባት የሞከሩ 10 የሸኔ ታጣቂዎች በኅብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሀላፊው ተናግረዋል።
በሀገር ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ የኅብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።