ትሕነግ ትምህርት ቤቶችን የአስከሬን ማከማቻና ምሽግ አድርጎ እንደከረመ የሚያሳዩ መረጃዎች በስፋት እየወጡ ነው

ታኅሣሥ 19/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ኃይል ትምህርት ቤቶችን የአስከሬን ማከማቻ፣ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ስፍራና ምሽግ አድርጎ መክረሙን የሚያመለክቱ መረጃዎች በስፋት እየወጡ ነው፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የወገል ጤና የ2ኛ ደረጃና ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን አሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ኃይል የአስከሬን ማከማቻ አድርጎት እንደከረመ ተገልጿል፡፡

የሽብር ቡድኑ ትምህርት ቤቱን በማውደምና በመዝረፍ የመማር ማስተማር ሥራ እንዳይሰራበት አድርጎት እንደሄደ ዋልታ በስፍራወ ተገኝቶ ተመልክቷል።

በደቡብ ወሎ ወገል ጤና ከተማ የሚገኘው ትምህርት ቤቱ በሽብር ቡድኑ መውደሙ በትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይም ከባድ የስነ ልቦና ጫና እንዳደረሰባቸው ተማሪዎቹ ለዋልታ ገልፀዋል።

በ1968 የተመሰረተውን ትምህርት ቤት የሽብር ቡድኑ የወታደራዊ መለማመጃና የአስከሬን ማከማቻ አድርጎት እንደከረመ ነው የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አሰፋ ጌቱ ለዋልታ የገለፁት፡፡

በግቢው ምሽግ ሰርተው እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡

አረመኔው ቡድን የትምህርት ቤቱን ወንበር በእሳት እንዲጋይ አድርጓል፤ የቤተሙከራ መሳሪያዎችን እና  የቤተ መጽሐፍት ንብረቶችን ሁሉ አውድሟል፡፡

ምንይሉ ደስይበለው (ከወገል ጤና ከተማ)