ትሕነግ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይዳረስ እንቅፋት መሆኑን እንግሊዝ አስታወቀች

በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለተጎጂዎች ለማቅረብ ቢታሰብም የሽብርተኛው ትሕነግ ወራሪ ቡድን እንቅፋት እንደሆነ የእንግሊዝ መንግሥት አስታውቋል።
የእንግሊዝ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ አማካሪ ሽብርተኛው ትሕነግ ወርሯቸው የነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎችን የጎበኙ ሲሆን፣ ጦርነቱ ንፁሃንን ለሞት፣ ለእንግልት እና ለስደት መዳረጉን ገልጸዋል።
አሸባሪው ቡድን በወረራቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ንፁሃን ዜጎችና ምንም የማያውቁት እንስሳትም ጭምር ተገድለዋል፤ በርካታ ወገኖች ለአካል ጉዳት እና ለስደትም ተዳርገዋል፤ መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል።
“ይህን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በአካል ሄደን በዓይናችን አይተናል፤ አዝነናልም” ብለዋል ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት አማካሪው ኒክድል፡፡
ሚስተር ኒክድል ሕጻናት ጭምር ለሞት እና ለጉዳት መዳረጋቸውን አንስተዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት ለማንም የማድላት ፍላጎት የለውም ያሉት አማካሪ፣ ተቀዳሚና መሠረታዊ ትኩረቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
አፋጣኝ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ለመድረስ ሽብርተኛው ትህነግ የጦርነት ትንኮሳውን ማቆም አለበት ብለዋል፡፡
ይህ ካልሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚቸገሩና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ዓለም አቀፍ ሕጎች ሊከበሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለተጎጅዎች ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል መንግሥታቸው የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።