ትዴፓ አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በህጻናትና ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ አወገዘ

ነሀሴ 4/2013 (ዋልታ) –  አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በህጻናትና ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ እንደሚያወግዝ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል በፈጸመው ጥቃት 107 ሕጻናትን ጨምሮ 240 ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን አልጀዚራ በሰራው ዘገባ ማጋለጡ ይታወሳል፡፡

ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት በአፋር ክልል “ካሊኩማ” በሚባል ሥፍራ የሚገኙ ከተማዎችና ትምህርት ቤቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ምንም እንኳን መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም አሸባሪው ሕወሓት በአጎራባች ክልሎች ላይ የሚያደርገውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ዘገባው አካቷል።

አሸባሪ ቡድኑ በአፋር ክልል ላካሄደው የሽብር ጥቃት ሕፃናትን ማሰለፉንም ዘገባው አውስቷል።

የሽብር ጥቃቱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውም ተመልክቷል፡፡

ትዴፓ አሸባሪው ቡድን በንጹሃን ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ መሆኑንና በተፈጸመው ድርጊትም በእጅጉ ማዘኑን አስታውቋል፡፡

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉብርሃን ኃይሌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ አሸባሪው ከዚህ ቀደም ሲፈጽመው የቆየውን ድርጊት አሁንም መድገሙ አሳዝኗቸዋል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን “ከትግራይ በቀለ እንጂ ፍጹም የኢትዮጵያና ትግራይ ስነ-ልቦና የሌለው” ነው ያሉት ሃላፊው፤ ቡድኑ እስኪጠፋ ድረስም ይህን ድርጊት ሊያቆም የማይችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሽብር ቡድኑ መጥፋትና መደምሰስ በጋራ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በደረሰው ጥፋት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለአፋር ህዝብና መንግስት ገልጸዋል፡፡

በመንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ አሸባሪ ቡድኑ የአገሪቱን ሠላምና ደኅንነት እያወከ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብ ተጠይቆ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በቅርቡ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወርም የአሸባሪው ሕወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውም ይታወሳል፡፡