ትዴፓ የትግራይ ወጣት በውል በማይታወቅ ዓላማ-ቢስ ጦርነት እንደ ቅጠል እየረገፈ እንደሚገኝ ገለጸ

ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) የትግራይ ወጣት ይኸ ነው ተብሎ በውል በማይታወቅ ዓላማ-ቢስ ጦርነት ተገዶ እየገባ እንደ ቅጠል እየረገፈ ይገኛል ሲል ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ገለጸ፡፡

ፓርቲው የካቲት 11ን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን ወገናችን በሆነው የአማራና የአፋር ሕዝብ ጭምር እየደረሠ ያለውን መከራ ምንጩ የሕወሓት አመራር እንደሆነ አመላክቷል።

የትግራይ ሕዝብ በሀገሩ ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ዜጋ መብቱ ተከብሮለት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተስማምቶና ተደጋግፎ መኖር ከፈለገ ነቀርሳውን የሕወሓት አመራር ማስወገድ እንዳለበትም አሳስቧል።

የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም የትግራይ ሕዝብ ብሔራዊ መብቱ የሚከበርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትኖር ዘንድ፣ ሕወሓት ፀረ-ደርግ እና መሠሎቹ ትጥቅ ትግል የጀመረበት ቀን እንደነበረ ያስታወሰው ፓርቲ ለዚህ በጎ ዓላማ አያሌ ወጣቶች መስዋእት ሲሆኑ ሕዝቡም ሠላምና ዕድገት አገኛለሁ በሚል እሳቤ ብዙ መከራ ማሳለፉን አመልክቷል።

ሆኖም ግን ከ47 ዓመታት በኋላ የትግራይ ሕዝብ መከራ ከያኔው ጊዜ ብሶበት ብቻ ሳይሆን በታሪኩ አጋጥሞት የማያውቀው ፖለቲካዊ፣ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ስብራት ውስጥ መግባቱ የሚያሳዝን ነው ብሏል።

ይኸንን መራራ ሀቅ ማገናዘብ ያልቻሉና የሕዝቡ መከራ የማይሠማቸው የሕወሓት አመራር እና ግልብ ተከታዮቻቸው «የካቲት 11» የህዝቡን ጥያቄ የመለሠ አውደ ቀን አስመስሎ በማቅረብ ከበሮ ሲደልቁ፣ ሲጨፍሩ እና ሲያስጨፍሩ ይታያሉ ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

እንደ እውነቱ ከሆነ የትግራይ ሕዝብ ያለበት ሁኔታ አዕምሮ ላለው ሠው የሚያሳዝንና ልብ የሚያቆስል እንጂ ጭፈራ የሚያስወጣ ቅንጣት ታክል ምክንያት የለውም ሲልም አክሏል።

በትግራይ ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን ወገናችን በሆነው የአማራና የአፋር ሕዝብ ጭምር እየደረሠ ያለውን መከራ ምንጩ የሕወሓት አመራር እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል ያለው ትዴፓ ይኸ ቡድን ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በአምባገነንት ሲመራ፣ ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያን የድኅነት መቀመቅ የከተተ፣ ሕዝቡ ባልረባ ምክንያት እርስ በራሱ እንዲጋጭ ከዛ አልፎም እንዲገዳደል ያደረገ፣ በስግብግብነትና በመሠሪነት የተካነ መወገድ ያለበት ቡድን መሆኑን ይገነዘባል ብሏል።