ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ዜጋ እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ

የትግራይን ክልል መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት መላው ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ትብብርና እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ጥሪ አቀረቡ።

ዋና ስራ አስፈፃሚው ትላንት ምሽት በባህርዳር ከተማ የአማራ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ሽኝት ላይ እንዳሉት የትግራይ ህዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ለዘመናት ለኢትዮጵያ አንድነት ሲታገል የኖረ ነው።

በተለይም የአማራና የትግራይ ህዝብ በማንኛውም መንገድ ሊለያይ የማይችል እርስ በእርስ የተዋለደና በባህል በሃይማኖት የተሳሳረ አንድ ህዝብ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በህወሓት የአመራር ዘመን ከመደጋገፍና መተጋገዝ ይልቅ መገፋፋት በርትቶ መቆየቱን ገልጸው፣ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገቢ አለመሆኑን ያምናል” ሲሉ አክለዋል።

“የህወሓት ጁንታ መሪዎች በፈጠሩት ችግርም የትግራይ ህዝብ ባላሰበውና ባልገመተው ሁኔታ ከማንም በላይ ለከፋ ችግር ተጋልጧል” ብለዋል።

ጁንታው አሁንም ቢሆን የወሰንና መሰል አጀንዳዎችን በማንሳት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እግሩን እንዳይተክልና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጁንታውን የማስወገድ ዋናው ስራ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሁንም መልሶ የማደራጀትና ፈታኝ የህግ ማስከበር ስራዎች እንዳሉ ዶክተር ሙሉ አብራርተዋል።

“በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን የትግራይን ህዝብ መልሶ ለማደረጀት በሚደረገው ርብርብ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው” በማለት ለዚህም የቀደመ የመተባበርና የመተጋገዝ ባህላችን መሰረት ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ በኋላ በሃይልና በጉልበት እኔ አውቅልሃለሁ የሚባልበት ጊዜው አልፏል ያሉት ዶክተር ሙሉ በሚገጥሙ ጉዳዮች ዙሪያ በጠረጴዛ ዙሪያ በህግና ስርዓት በውይይት ይፈታል ብለዋል።

የትግራይ መንግስት መልሶ እንዲዋቀር ማገዝ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዴሳ ናቸው።

ጁንታው በፈጠረው ችግር የትግራይ ህዝብ አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“ለዚህም የክልሉን መንግስት መልሶ በማቋቋም የህዝብ ጥያቄ የሚያስተናግድ ሃይል እንዲኖር ጊዜያዊ አስተዳደሩን በቁርጠኝነት መደገፍ ይገባል” ብለዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው፣ “የትግራይ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር መስዋትነት የከፈለ ታላቅ ህዝብ ነው” ብለዋል።