ሐምሌ 02/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ የሚገቡ ከትግራይ ወደ ውጭም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች የሚደረጉ ሁሉም በረራዎች በቅድሚያ ቦሌ አየር ማረፊያ ማረፍ እንዳለባቸው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአውሮፕላኖች ላይ አስፈላጊ ፍተሻ እንደሚደረግ እና የተናጠል ተኩስ ማቆም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እ.ኤ.አ ከሰኔ 23 ቀን 2013 ጀምሮ የሰሜን የአየር ክልል ከ290 በታች የበረራ ደረጃ ዝግ ቢያደርግም እ.ኤ.አ ከሰኔ 25 ቀን 2013 ጀምሮ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው አካላት ልዩ የበረራ ፍቃድ መስጠቱ ይታወቃል፡፡
ከወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት በረራ ያልከለከለ መሆኑንና ትናንት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሁለት አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ በረራ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች ላይ መስተጓጎል እንደፈጠረ ተደርጎ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ትክክል አለመሆናቸውን ገልጾ የበረራውን ሁኔታ ለማቀላጠፍ ወደ ትግራይ በረራ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ፍቃድ ማግኘት አለባቸው ብሏል፡፡