ቻይና ለፕሬዝዳትን ኢሳያስ አፈወርቂ የጉብኝት ግብዣ አቀረበች

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) የቻይናው ፕሬዝዳት ሺን ጂንፒንግ ለኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ የጉብኝት ግብዣን አቀረቡ፡፡
ግብዣው የቀረበላቸው የፕሬዝዳንቱን መልዕክት እና ልዑክ ይዘው በአስመራ በሚገኙት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በኩል ነው፡፡
ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በሺን ጂንፒንግ የተላከን ደብዳቤም አስረክበዋል፡፡
ደብዳቤው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ቤጂንግ አቅንተው በሁለትዮሽና ስልታዊ አጋርነት ዙሪያ ጥልቅ ውይይት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መሆኑን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በቲውተር ገጻቸው አሳውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው የቻይናን የ100 ዓመታት የጋራ ተጠቃነት መርህ ጉዞ እና በዓለም ዐቀፍ ሕጎች ማዕቀፍ ውስጥ ሆና ዓለምን ሚዛናዊ ለማድረግ የምታደርውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የኤርትራን የልማት ፕሮግራሞች፣ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ጉዳዮች የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያላትን አተያይ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በምፅዋና አሰብ ወደቦች ልማት፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በመሰረተ ልማትና ማዕድን ዘርፍ ትብብራቸውን ለማላቅ ተስማምተዋል፡፡