ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – ቻይና በሰብዓዊ መብቶች ሰበብ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረጉ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደምትቃወም የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት የኢትዮጵና የቻይና ስትራቴጂክ ግንኙነት በብዙ መንገድ ፍሬያማና በጠንካራ ትብብር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አድንቀዋል።
በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሃት የተናጥል ተኩስ አቁሙን በመጣስ በአጎራባች አማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን ፣ የግለሰቦችንና የመንግስት ንበረቶችን ማውደሙን አስታውቀዋል።
ቻይናም ይህንን የሽብር ተግባር አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዝ ጥሪ እንድታቀርብ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቱኒዚያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ለፀጥታው ምክር ቤት ለማቅረብ ያደረገችው ሙከራ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ቻይና ጉዳዩን የአፍሪካ ህብረት በሚመራው ሁኔታ እንዲቀጥል ድጋፏን እንደምታደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮችን በራሷ የመፍታት ሉዐላዊ መብቷን ታከብራለች በማለት ገልጸዋል።
በሰብአዊ መብት ጥበቃ ሰበብ በውጭ ሃይሎች የሚደረጉ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶችንም ቻይና ትቃወማለች ሲሉ ነው የገለጹት።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ አፈጻጸምን በተመለከተ ቻይና በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለሚታይበት ሁኔታ የማያቋርጥ ድጋፏን ትሰጣለች ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ በልዩ ልዩ ሀሉትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።