ቻይና በድርቅ ለተጎዱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደምታደርግ ገለጸች

የካቲት 22/2014 (ዋልታ) ቻይና በድርቅ ለተጎዱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሶማሌያው አቻቸው አብዲሰይድ ሙሴ አሊ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት እንዳስታወቁት ቻይና በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው የአካባቢው አገራት አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ታደርጋለች።

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ድጋፍ የሚደረግላቸው አገራት መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት እንዲመጣ ቻይና የምታደርገው ተግባራዊ ድጋፍ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቻይና ከአካባቢው አገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነትና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ልዩ መልዕክተኛ መድባ ወደ ሥራ መግባቷን ማስታወሳቸውን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።