ቻይና ታይዋንን የምትወር ከሆነ አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን እንደምትፈጽም አስታወቀች

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) ቻይና ታይዋንን የምትወር ከሆነ አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን እንደምትፈጽም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ፡፡

በጃፓኗ ዋና ከተማ ቶኪዮ በጉብኝት ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ባይደን እንደገለጹት ቻይና በጉልበት ታይዋንን ለመጠቅለል ከተንቀሳቀሰች አገራቸው ለታይዋን ወታደራዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ጣልቃ ትገባለች፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ዛሬ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጋር በጋራ መግለጫ እየሰጡ ባሉበት ሰዓት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡

ታይዋንን ከቻይና ወረራ ለመታደግ ሀገርዎ ዝግጁ ናትን? ተብለው የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ባይደን ፈርጠም ብለው “መጠርጠሩስ” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ባይደን ምላሻቸውን ሲቀጥሉም እኛ የቻይናን አንድነትን ፖሊሲ ፖሊሲ የምናምንበት እና የፈረምንበት ቢሆንም ነገር ግን ቻይና ጉልበትን ተጠቅማ የቀድሞ ግዛቷ የሆነችውን ታይዋን ለመጠቅለል ከተንቀሳቀሰች ምላሻችን በተመሳሳይ ጉልበት ይሆናል ብለዋል፡፡

የአንድ ቻይና ፖሊሲ ታይዋን የቻይና አንድ አካል እንደሆነች የሚገልጽ እና አሜሪካም የምትስማማበት ቢሆንም የአሜሪካ ባለስልጣናት ግን በታይዋን ጎዳኖች ላይ የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት የመከላከል አቋም እና ግዴታ አለባት ብለዋል፡፡

የታይዋኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ቻይና በታይዋን ላይ የምታካሂደውን ወረራ አሜሪካ እንደምትከላከል ፕሬዚዳንት ባይደን በመግለጻቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ቻይና በበኩሏ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ለባይደን ንግግር በሰጠችው አፋጣኝ ምላሽ በፕሬዚዳንት ባይደን ንግግር ክፉኛ ማዘኗን ገልጻ “በሉአላዊነቷ ላይ የሚደረጉ መሰል ጣልቃ ገብነቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ አይደለሁም” ብላለች፡፡

ሚኒስቴሩ አያይዞም አሜሪካ በአንድ ቻይና ፖሊሲ የተስማማች እና የፈረመች አገር ሆና ሳለ የቻይናን ሉአላዊነት በሚጻረር አቋም መያዟ አግባብ እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡

ማንኛውም አካል ለቻይና እና ለህዝቧ ጥንካሬ፣ ቁርጠኝነት፣ ጽኑ ፍላጎት እና የማድረግ አቅም ዝቅተኛ ግምት በመስጠት እንዳይሳሳት ሲል መክሯል፡፡ ሚኒስቴሩ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን የቻይና ህዝብ ጋር በተጻራሪው መቆም ዋጋ እንደሚያስከፍልም አስጠንቅቋል፡፡ በነስረዲን ኑሩ