ነሐሴ ከባድ መጠን ያለዉ ዝናብ የሚዘንብበትና ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚከሰትበት ወር መሆኑን ኢኒስቲትዩቱ ገለጸ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) በቀጣዩ ነሐሴ ወር በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ለተከታታይ ሰዓታትና ቀናት የሚዘንብበት መሆኑ የወንዞች ሙላትና ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚከሰትበት ጊዜ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በሚቀጥለው ወር ከኦሮሚያ ክልል የምዕራብ፣ የምስራቅ እና የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ጂማ እና አዲስ አበባ ዙሪያ፤ አዲስ አበባ፤ ሁሉም የአማራ ክልል እና የትግራይ ዞኖች፤ እንዲሁም የአፋር ክልል ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይም ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

ከዚህም ሌላ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ከደቡብ ክልል ደግሞ የሀድያ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ የወላይታ፣ ጌደኦ ዞኖች፤ እንዲሁም የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይም ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ፤ ኢሉአባቦራ፤ ቡኖ በደሌ፣ አርሲ እና የምዕራብ አርሲ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፤ ድሬዳዋና ሐረሪ፤ ሁሉም የጋምቤላ ክልል ዞኖች፤ ከሶማሌ ክልል ሲቲ እና ፋፈን ዞኖች ከሚኖራቸው እርጥበት አዘል አየር ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል፡፡

በተጨማሪም ከሚጠበቀዉ ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጎርፍ፣ የወንዞች ሙላት እና የመሬት መንሸራተት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም በየአካባቢዉ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸዉ አካላት ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኢኒስቲትዩቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው የደመና ሽፋን መጨመር በስተቀር በአብዛኛው ደረቅ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።