ነባሩን የለገዳዲና ድሬ ግድብ እድሳትና ማሻሻያ የ11ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ50 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን እና ለአዲስ አበባ ከተማ ትልቁን የውሃ አቅርቦ ሲያከናውን የነበረው የለገዳዲ ግድብ ለማደስ የ11ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይንም 600 ሚሊዮን ብር ገደማ ስምምነት ከዊ ቢውልድ (ሳሊኒ) ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ ጋር ተፈረመ።

በስምምነቱ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት የድሬና የለገዳዲ የውሃ ማጠራቀሚያ ግድቦች ካለ በቂ ጥገና ሃምሳ ዓመት አገልግለዋል።በተጨማሪም ከሃምሳ ዓመት ላለፈ ግዜ እንዲያገለግሉን የጥገና የዲዛይን ማሻሻያ ሥራው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ ገልጸዋል።

አስቀድሞ ሁለቱም ግድቦች በሳልኒ ኩባንያ የተገነቡ መሆናቸው አሁንም የጥገናና የማሻሻያ ሥራው በነሱ በኩል ቢሰራ መልካም በመሆኑ ስምምነቱ ተፈርሟል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ዘሪሁን አባተ፤ ኩባኒያው የለገዳዲ ትርፍ የውሃ ማፋሰሻ በሮች፣ የአደጋ ጊዜ ውሃ መቆጣጠሪያ ፣ ከግድብ ወደ ማጣሪያ ጣቢያ የውሃ መውረጃ ጥገናና ማሻሻያ ሥራን ጨምሮ የድሬ ግድብ ደለል ማስወገጃ ጥገና እና ማሻሻያ ሥራን የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱን የፈፀሙት የዊቢዩልድ ፕሮጀክት ማናጀር ዞፒስ ፕሮጀክቱን በሚገባ የሚያውቁት በመሆኑ በወቅቱና በተባለው ጊዜ ስራውን አከናውነው እንደሚጨርሱም ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የማሻሻያ እና የጥገና ስራው 18 ወራት የሚፈጅ ሲሆን በአለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚከናወን ነው፡፡

የለገዳዲና ድሬ ግድቦች የከተማዋን 40 በመቶ አካባቢን የሚሸፍን አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የከንቲባ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡