ነገ “ለመስቀሉ እሮጣለሁ” በሚል ይካሄዳል የተባለው ሩጫ ሕጋዊ እውቅና እንዳላገኘ ተገለፀ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) በነገው ዕለት “ለመስቀሉ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል የተባለው ሩጫ ከሚመለከተው አካል ሕጋዊ እውቅና ያላገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ፖሊስ ነገ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም “ለመስቀሉ እሮጣለሁ” በሚል ምክንያት በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚካሄድ ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ይገኛል ብሏል።
የጎዳና ላይ ሩጫን ለማካሄድ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ እና ዝግጅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ በተለይ ከሚመለከተው አካል ሕጋዊ የእውቅና ፈቃድ ማግኘት ግዴታ ሆኖ እያለ በድንገት የጎዳና ላይ ሩጫ ለማካሄድ የሚደረግ እንቅስቃሴ በከተማው የፀጥታ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚፈጥር መሆኑን ኅብረተሰቡም ሆነ ሩጫውን አዘጋጅተናል የሚሉ አካለት እንዲገነዘቡ አሳስቧል፡፡
ሩጫው ይደረግበታል በተባለበት ቀን ቀድሞ የታቀዱ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ፕሮግራም የተያዘ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ እያስታወቀ የፀጥታ ኃይሉ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካለት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ በድንገት ሩጫ እናደርጋለን የሚሉ ወገኖች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ነው ያሳሰበው::
የተዛባ መረጃ የሚያስተላልፉ አካለት ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና ተቋሙ ያስተላለፈውን መልዕክት በመተላለፍ ለሚፈጠር ማንኛውም ችግር ሩጫውን እናስተባብራለን የሚሉ አካለት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!